ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ
ከWikipedia
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የወይዘሮ አብቺው እና የ ዳግማዊ ምኒልክ ልጅ ሲሆኑ ከልጅ ኢያሱ ቀጥለው በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የተቀመጡ መሪ ናቸው። አባታቸው የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ ዐፄ) ብ ስድስት ዓመት እድሜያቸው ለአሥራ ሁለት ዓመቱ የ ዐፄ ዮሐንስ ልጅ ለአርአያ ሥላሴ ተዳሩ። ጋብቻቸውም ጥቅምት 13 ቀን 1875 ዓ.ም በተክሊልና በቁርባን ተፈጸመ፡ የሠርጉም ማማርና የሽልማቱ ብዛት ሊነገር አይቻልም። ልጅ ኢያሱ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ከስልጣን ሲወርዱ፤ መኳንንቱ ወይዘሮ ዘውዲቱን ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት፤ ራስ ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እንዲሆኑ ወስነው የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም ዘውድ ጭነው ነገሡ። ለዘውዱ በዓልም በኢትዮጵያ አዋሳኝ ያሉት የእንግሊዝ ሱዳንና የእንግሊዝ ሱማሌ ገዥዎች፤ የፈረንሳይ ሱማሌ ገዥ እና በኢትዮጵያም ታላላቅ ራሶች እንዲሁም የየአውራጃው ገዥዎች በተገኙበት በዕለተ እሑድ በትልቁ ደብር በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግስት ተቀብተው የንጉሠ ነገሥቱን ዘውድ ጫኑ። ከዚህም በኋላ እንደ ሥርዓተ ንግሡ ሕግ፤ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በአባታቸው ዙፋን ተቀምጠው መንገሣቸውን፤ ደጃዝማች ተፈሪም ራስ ተብለው አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ መሆናቸውን በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት አዋጅ ተነገረ።
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በነገሡ በ አሥራ ሦሥት ዓመት ተኩል መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ዐርፈው አባታቸው ዐፄ ምኒልክ በተቀበሩበት በአታ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ።
[ለማስተካከል] ዋቢ መጻሕፍት
- ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ቀ.ኃ.ሥ 1929ዓ.ም - ገጽ 37-38
- አጤ ምኒልክ - ከጳውሎስ ኞኞ1984 ዓ.ም -ገጽ 77
- የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ 1999 ዓ.ም. ገጽ 136