ቡና
From Wikipedia
ቡና የተክል አይነትና ከዚህ ተክል ቡን የሚወጣው መጠጥ ነው። መጀመርያ የታወቀ በኢትዮጵያ ሲሆን በዓለሙ ልሳናት ስሙ የተነሣ ምናልባት ከድሮው ከፋ መንግሥት ሊሆን ይቻላል። በአንድ ትውፊት መሠረት በመጀመርያ ያገኘው ሰው ካልዲ የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ እረኛ ፍየሎቹ ፍሬውን በልተው ሲጨፍሩበት ነበረ።
በደራሲው ዊሊያም ኡከርስ መጽሐፍ 'ኦል አባውት ኮፊ' (ሁሉ ስለ ቡና) ኅልዮ ቡና ወደ የመን የገባው በአክሱም መንግሥት ዘመን በ517 ዓ.ም. አካባቢ ነበር። የፋርስ ሃኪም አል-ራዚ (857-917 ዓ.ም. የኖሩ) ተክሉን «ቡንቹም» ብሎት ምናልባት በታሪክ አንደኛው ስለ ቡና መግለጫ የመዘገበው ጸሐፊ ይሆናል። ደግሞ ሌላ ፋርስ ሀኪም እብን-ሲና (972-1029 ዓ.ም.) ስለ «ቡንቹም» ጥቅም ጽፏል። የሞሮኮ ደርቡሽ ሼክ አቡል-ሀሳን አሽ-ሻዲሊ (1167-1250 ዓ.ም.) በአሠብ ዙሪያ ሲጓዙ ኗሪዎች ስለ ቡና መጠጥ እንዳሳወቁት ይባላል። የአደን ሙፍቲ ሼክ ጃማል-አል-ዲን አል-ዳባኒ በ1446 ዓ.ም. ገዳማ መጀመርያ መጠቱን እንዳስገባ ይመዘገባል። በ1449 ዓ.ም. መጀመርያው ቡና ቤት «ኪቫ ሃን» በኢስታንቡል ቱርክ ተከፈተ።
ሆኖም በ1503 ዓ.ም. የማካህ ይማሞች ቡና ቤት ስላልወደዱ መጠጡን ሃራም (እርም) አሉት[1]። ነገር ግን የኦቶማን ቱርክ ሡልጣን 1 ሰሊም በ1509 ዓ.ም. ማካህን ይዘውት በ1516 ዓ.ም. ይህን ድንጋጌ ገልብጠው የተቀደሰ መጠት አደረገው። ከዚያ በኋላ እስላሞች በተለይ ቡናን ስለወደዱት፣ ለኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እስከ 1881 ዓ.ም. ድረስ እንደ ተከለከለ ዛሬ በሰፊ አይታወቅም። ከ1872 እስከ 1878 ድረስ ቡና መጠጥ በኢትዮጵያ ቶሎ ስለ ተስፋፋ አጼ ምኒልክ ቢሆኑም ስለ ጠጡት በ1881 ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ሆነው አቡነ ማቴዎስ 10ኛ ቡናን አጸደቁት።
አረቦች በ16ኛ ክፍለ ዘመን ተክሉ ከአረብ እንዲወጣ ምንም ባይፈቅዱም አንዳንድ ሰው ወደ ውጭ አገር በስውር የቡና ዘር ይዞ ከአረብ አመለጠ።